13ቱ ሕማማተ መስቀል
13ቱ ሕማማተ መስቀል
ሕማም ማለት ሐመ ካለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጓሜውም ሕመም፣ መከራ ስቃይ ፣እንግልት ማለት ነው ። ቅድስት ቤተክርስቲያንም ይህን ሳምንት ሰሞነ ሕማማት ብላ በየዓመቱ ታከብረዋለች የሕማማት ሳምንት ማለቷ ነው::
1, ተኰርዖተ ርእስ /ራስና በዘንግ መመታት/
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን በዘንግ መመታቱንና መቀጥቀጡን የሚገልጥ ነው፡፡ “ተኰርዖት” የሚለው ቃል ኩርዐ – መታ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ ርእስ ደግሞ ራስ ማለት ነው፡፡ አገረ ገዥው ጲላጦስ “ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተላልፎ ከተሰጠ በኋላ የእሾህ አክሊል ጐንጉነው ራሱ ላይ ደፍተውበታል፡፡ ራሱንም በዘንግ መትተውታል /ማር 15፥19/፡፡
2, ተፀፍዖ መልታሕት /በጥፊ መመታት/
አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እጃቸው በደም፣ ጣቶቻቸው በበደል በረከሰ በአይሁድ እጅ በጥፊ መመታቱን የሚገልጥ ነው፡፡ “ተፀፍዖ” የሚለው ቃል ፀፍዐ በጥፊ መታ ከሚለው የግእዝ ግሥ የወጣ ነው፡፡ መልታሕት ደግሞ ፊት ጉንጭ ማለት ነው፡፡ ጌታችን ለሊቀ ካህናት ቀያፋ እውነትን መናገር እንደ ስድብ ተቆጥሮበት መላልሰው ፊቱን በጥፊ መትተውታል፡፡ ፊቱንም በጨርቅ ሸፍነው “ክርስቶስ ሆይ በጥፊ የመታህ ማነው? ትንቢት ተናገርልን” እያሉ ዘብተውበታል፡፡ /ማቴ 27፥27/፡፡ ጲላጦስ አሳልፎ ከሰጠው በኋላም አክሊለ ሦክ በራሱ ላይ አኑረው ቀይ ልብስ አልብሰው “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፣ ሰላም ለአንተ ይሁን” እያሉ እየተሳለቁበት በጥፊ መትተውታል / ዮሐ 19፥2-4/፡፡
3,ወሪቀ ምራቅ /ምራቅ መተፋት/
ርኩሳን አይሁድ በብርሃናዊው የክርስቶስ ፊት ላይ በሚያስጸይፍ ሁኔታ ምራቃቸውን እንደተፉበት የሚገልጥ ነው፡፡ “ወሪቅ” የሚለው ቃል ወረቀ ካለው ግእዛዊ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ ትርጉሙም እንትፍ አለ፣ (ተፋ) ማለት ነው፡፡ በነቢዩ በኢሳይያስ መጽሐፍ “ፊቴንም ከውርደትና ከትፋት አልመለስኩም” ተብሎ እንደተነገረ እየዘበቱበት ምራቃቸውን ተፉበት /ኢሳ. 50፥6፣ ማቴ 27፥29-3ዐ፤ ማር 15፥19/፡፡ በኃጢአት የቆሸሸውን የሰውን ሕይወት ለማጥራት የመጣው ንጹሐ ባሕርይ አምላክ ተተፋበት፡፡ በሥራው ከገነት ተተፍቶ፤ ተንቆ፤ ተዋርዶ የነበረውን የሰውን ልጅ ለማዳን ኃጢአትን ይቅር የሚል እርሱ ጌታችን ያለ ኃጢአቱ ተተፋበት፤ ተናቀ፤ ተዋረደ፡፡
4,ሰትየ ሐሞት /መራራ ሐሞት መጠጣት/ ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል ሳለ ተጠማሁ ባለ ጊዜ መራራ ሐሞት መጠጣቱን የሚገልጥ ነው፡፡ “ሰተየ” ማለት ጠጣ ማለት ነው፡፡ ሐሞት የሚለውም አሞት ተብሎ በቁሙ ይተረጐማል፡፡ በመዝሙር 68 ቁጥር 21 ላይ “ለመብሌ ሐሞት ሰጡኝ፣ ለጥማቴም ሆምጣጤ አጠጡኝ” ተብሎ የተነገረውም የነቢዩ የዳዊት ትንቢትም ተፈፀመ አርባ ዓመት ሙሉ በቃዴስ በረሃ ኳትነው ለነበሩ አባቶቻቸው ከሰማይ መና አውርዶ የመገባቸው፤ ከአለት ላይ ውኃ አፍልቆ ያጠጣቸው ክርስቶስ በተጠማ ጊዜ ቀዝቃዛ ውኃ ነፈጉት /ዘዳ 16፥1-2ዐ፤ 1ቆሮ 1ዐ፥3/፡፡ የዝናባት፤ የባሕርና የውቅያኖስ ጌታ በውኃ ጥም ተቃጠለ፡፡
5, ተቀሥፎ ዘባን /ጀርባን መገረፍ/
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጀርባውን ሥጋው አልቆ አጥንቱ እስኪቆጠር ያለ ርኅራኄ የመገረፉን ነገር የሚገልጥ ነው፡፡ “ተቀሥፎ” የሚለው ቃል ቀሠፈ- ገረፈ ካለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ “ዘባን” ደግሞ ጫንቃ፣ ትከሻ፣ ጀርባ ማለት ነው፡፡ በአይሁድ ሕግ የተገረፈ አይሰቀልም፡፡ የሚሰቀል ደግሞ አይገረፍም ነበር፡፡ ጲላጣስ ግን ኢየሱስ ክርስቶስን አስገረፈው፡፡ ከደሙ ንጹሕ ነኝ ብሎ ከታጠበ በኋላ ክርስቶስን ያለ ኃጢአቱ በመግረፍ ለአይሁድም አሳልፎ ስጠው /ማቴ 27፥28፤ ማር 15፥15፤ ዮሐ19፥1/፡፡ በነቢዩ በኢሳይያስ “ጀርባዬን ለገራፊዎች፣ ጉንጬንም ለጠጉር ነጪዎች ሰጠሁ” /በኢሳ 5ዐ፥6/ ተብሎ እንደተነገረ ጀርባውን ለገራፊዎች አሳልፎ ሰጠ፤ ጽሕሙንም ተነጨ፡፡
6,ተዐርቆተ ልብስ /ከልብስ መራቆት/
አምላካችን ኢየሱስ ክርስስቶስ ልብሱን መራቆቱን የሚገልጥ ነው፡፡ “ተዐርቆተ” ማለት ታረዘ፤ ተራቆተ ማለት ነው፡፡ ፀሐይና ከዋክብትን ብርሃን አልብሶ የፈጠረ አምላክ ተራቆተ፡፡ ጸጋውን ለዕሩቃን የሚያለብስ አምላክ ልብሱን ተገፍፎ ዕራቁቱን ቆመ፡፡
7, ርግዘተ ገቦ /ጎንን መወጋት/
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ከሰጠ በኋላ ጎኑን በስለታም ጦር መወጋቱን የሚገልጥ ነው፡፡ “ርግዘት” የሚለው ቃል ረገዘ- ወጋ ከተሰኘ የግእዝ ግሥ የወጣ ነው፡፡ ገቦ ማለት ደግሞ ጎን ማለት ነው፡፡ መሞቱን ለማረጋገጥ ከጭፍሮቹ አንዱ አንድ ዓይኑ የጠፋ ሌንጌዎስ የተባለ ወታደር ጎኑን በጦር ስለወጋው ወዲያው ከጎኑ ደምና ውኃ ፈሰሰ /ዮሐ 19፥33/፡፡ ከጉነ የወጣው ውኃ የወታደሩን የጌንጊዮስን አንድ ዓይን አበራለት ለኛ ለልጆቹም በጥምቀት የልጅነት ፀጋ ሰጠን
8, ኅሪት /ወደ ኋላ መታሠር/
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት እጆቹን ወደኋላ የፊጥኝ መታሠሩን የሚገልጥ ነው፡፡ “ተአሥሮት” የሚለው ቃል አሠረ (ሲነበብ ይላላል) ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም አሠረ ማለት ነው፡፡ “ድኅሪት” የሚለው ቃል ደግሞ ተድኅረ- ወደኋላ አለ ከሚለው ግሥ የወጣ ነው፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጊዜው በደረሰ ሰዓት ራሱን ለአይሁድ አሳልፎ በሰጠባት በዚያች ዕለትና ሰዓት ሻለቃውና ጭፍሮቹ የአይሁድም ሎሌዎች እጁን የኋሊት አሥረው መሬት ለመሬት ጎትተውታል፡፡ አፍገ ምግመውታል /ዮሐ 18፥12/፡፡ በኃጢአት ሰንሰለት የኋሊት ታሥሮ ጠላት ዲያብሎስ የሚያፍገመግመውን የሰው ልጅ ለማዳን፣ ሰውንም ከኃጢአት እሥራት ይፈታ ዘንድ ሲል መድኃኔዓለም ክርስቶስ በጠላቶቹ በአይሁድ እጅ የኋሊት ታሠረ፡፡ ቀሪዎቹ 5ቱ ሕማማት ደግሞ” አምስቱ ቅንዋተ መስቀል ይባላሉ “ቅንዋት” የሚለው ቃል ቀነወ- ቸነከረ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ነው ቅንዋት ሲሆን ደግሞ ችንካሮች ይሁናል እነዚህ ችንካሮች የብረት ሚስማሮች ናቸው ስማቸውም
9,ሳዶር፣
10,አላዶር፣
11,ዳናት፣
12,አዴራ፤
13,ሮዳስ የተባሉ ይባላሉ፡፡ እነዚህም የአምሥቱ አዕማደ ምሥጢራት ምሳሌዎች መሆናቸውን አበው ያስተምራሉ፡፡ እንዴት ቢሉ ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ስቦት ለሰው ልጅ ሲል በእነዚህ የችንካር ሚስማሮች እንደተቸነከረ 5ቱ አዕማደ ሚስጢራትንም የሃይማኖት አምድ( ምሶሶዎች) ናቸውና ጠንቅቆ ለተማራቸው የወንጌል ችንካሮት ሆነው ልብን ወግተው በሃይማኖት የሚያፀኑ(የሚቸነክሩ)በምግባር የሚቀኑ በመሆናቸው ነው ለዚህም አይደል ሐዋርያው ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየኝ ማነው? ብሎ የተናገረው ሮሜ 8÷35