Home Events ትንሳዔ (ፋሲካ )
Loading Events
  • This event has passed.
  • STARTApr 24th - 12:00am

  • ENDApr 24th - 11:59pm

  • VENUE

ትንሳዔ (ፋሲካ )

“ወምድርሰ ሀለወት እራቃ ወኢታስተርኢ ወኢኮነት ድሉተ ወጽልመት መልዕልተ ቀላይ ወመንፈሰ
እግዚአብሔር ይጼልል መልዕልተ ማይ”(ዘፍ ፩፡፪) በጥልቁ ጨለማ የነበረች ዓለም፥ ሕይወት ለማመንጨት
የእግዚአብሔር መንፈስ በውሀው ላይ እንደንዣበበ፥ “ናሁ ይመጽእ በደመና ሰማይ ወትሬእዮ ኩሎ ዓይን”(ራዕ
፩፡፯):: ክርስቶስም ሙታንንን ለማንሣት በሕይወት ሰጭና ሙታንን በሚቀሰቅስ ደመና አንዣቦ ይመጣል::
“ወመጻት ደመና ብርህት ወውስተ ደመና ይነብር ወልደ እጓለ እመሕያው”(ራዕይ ፲፬፡፲፬):::: እንዲል ክርስቶስ
የሚመጣበት ደመና አፈር ትቢያ የሆነውን የሰውን አካል ለመቀሰቅስ መለኮታዊ ኃይል አለው ይሉና፥ ከባሕርና
ከቀላይ የሚነሣው ደመና አፈር ትቢያ የሆነውን ሰርዶ የሚያለመልም፥ የነበሩበት ውኀ ሲደርቅ ወደ አፈርነት
የተለወጡትን እንቁራሪቶች የሚቀሰቅስ ከሆነ፥ ክርስቶስ ተጭኖ የሚመጣበት ደመና አፈር ትቢያ የሆነውን ሰብአዊ
አካል ቀስቅሶ ማስነሣት መቻሉን መጠራጠር እንደሌለብን ሊቃውንት ይናገራሉ::

ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት አበው እነ ኤጲፋንዮስ ስለ ትንሣኤ ሲናገሩ፥ በደመና የሚንቀሳቀሱትን
ተሐዋስያንና አዝርእቶችን እንደምሳሌ ጠቅሰዋል:: “ወአንበጣሂ እምድኅረ ሞተ ይትነሣእ እምነ ምድር::
እምልደት ዘወጽአ እምኔሁ:: ወፍሬያትሂ ይዘርዑ ወይመውቱ ቅድመ ውስተ ምድር:: ወእምድኅረ ዘመን ታወጽእ
ምድር ዘቀበረት ውስቴታ ወለእመሂ ኢሞቱ ኢየሐይው” (ሃይ ምዕ ፶፰፡፯) ብለዋል:: ይህም ማለት በወቅቱ
የሕይወት ደመና በመሬት ላይ ሲያንዣብብ የሞተው የበሰበሰው አንበጣ ከምድር እንደሚፈላ፥ ክርስቶስ በደመና
ተጭኖ ሲመጣ አፈር ትቢያ ሆኖ እባቡ ሲልሰው የነበረው ሁሉ ሰባዊ አካል ከምድር ይነሣል::
ከክርስትና በፊት “መቃብራችሁን እከፍታለሁ:: ከመቃብራችሁም አወጣችኋለሁ” (ሕዝ ፴፯፡፲፪)::
እየተባለ በነብያት ሲነገር ኖሯል:: ከነብያት ወዲህ ክርስቶስ ሊወለድ አቅራቢያ “የሚሞቱ ሰዎች መነሳታቸውን
ካላመንክ ከእናት ከአባታቸው ሳይወለዱ በክረምት ከየቦታው የሚፈሉትን ፍጥረታት ተመልከት”(ሣል መቃ
፲፡፩):: እየተባለ ስለ ሰው ልጅ ትንሣዔ በተለያዩ ምሳሌዎች ተደጋግሞ ተነግሯል:: “የስንዴም ሆነ የገብስ
ሌሎችም በምድር የሚዘሩት ሁሉ ቅንጣት ካልሞቱና ካልበሰበሱ አይበቅሉም”(ቀዳ መቃ ፰፡፳፪) እየተባለ
ተገልጿል:: ጊዜው ሲደርስ “እውነት እውነት እላችኋለሁ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን
ትቀራለች:: ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች” (ዮሐ ፲፪፡፳፬):: እያለ የሕይወት ባለቤት ክርስቶስ ስለትንሣዔ
መኖር አረጋገጠ:: ጊዜው ደርሶ ክርስቶስ ሞትን ድል ነሥቶ የተናገረው የመጀመሪያ ቃሉ “ተውህበ ሊተ ኩሉ
ኩነኔ ሰማይ ወምድር”(ማቴ ፳፰፡፲፰):: የሚል ነው:: ማለትም፦ በሰማይና በምድር ስልጣን በእጄ ገባ ብሎ ነው::
ቅዱስ ጳውሎስም፥ “አንተ ሞኝ አንተ የምትዘራው ካልሞተ ሕያው አይሆንም”( ፩ኛ ቆር ፲፭፡፴፮):: እያለ
አጠንክሮና አረጋግጦ ስለትንሣዔ ያስተማረው ከዚህ ተነሥቶ ነው:: በመቀጠልም ቅዱስ ጳውሎስ “ወእምዝ ይሰአር
ደኀሪ ጸላኢ ዘውእቱ ሞት”(፩ኛ ቆሮ ፲፭፡፳፮):: እያለ አጠንክሮና አስረግጦ አስተማረ:: ማለትም፦ከእንግዲህ
ወዲህ ጠላታችን ሞት ተሽሯል:: “ዘይሔድስ ሥጋነ ትሑተ ወይሬስዮ አምሳለ ሥጋ ስብሐቲሁ በከመ
ረድኤቱ”(ፊል ፫፡፳፩):: በመሬትና በእባቡ ላይ የተሰነዘረው መርገም ተፈጸመ:: በሰው ላይ የተሰነዘረው የሩቅ
ዘመን የመቃብር ቆይታ ከወደቅንበት ለማንሣት በነበረው እቅዱ በትንሣዔው ኃይል አድሶ ያነሣን ዘንድ
ለትንሣዔያችን በኩር ሆነን:: እያለ ሰበከ::

ክርስቶስ ስልጣን ተሰጠኝ ብሎ የተናገረውን፥ ሐዋርያት በሰፊው ካስተጋቡት አዋጅ በመንደርደር፥ የነገረ
መለኮት እውቀት መሠረቶች ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት እነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “ወበከመ ከይሲ ዘኮነ
ያመልክዎ ሰብአ ባቢሎን ሶበ ውህጠ መብልዐ ዘመጠዎ ነቢይ ተሠጥቀ እማእከሉ ከማሁ ተሰጥቀ ሞት ሶበ ውህጠ
ሥጋሁ ለእግዚእ፥ ወሶበ ውህጠ ውእተ ሥጋ ቅዱሰ ሠጠቀ ከርሶ ወተንሥአ እሙታን ሕያወ” (ሃ.አ. ፷፯፡፲፰)::
በማለት የሰው አቅም በሚረዳላቸው በተለያዩ ምሳሌዎች እያረጋገጡ አስተማሩት:: ማለትም የባቢሎን ዘንዶ
ዳንኤል ያዘጋጀውን ሥጋ በዋጠ ጊዜ፥ እንደ ሌላው ሰው አካል የሚውጠው መስሎት፥ የጌታን ሥጋ ውጦ
መቃብር ተሰነጠቀ ሞትም እንደ ዘንዶው ፈነዳ:: በእባብና በሰው መካከል የነበረው ዘላለማዊ የተበይና የበይነት
ግንኙነት ፈረሰ:: እባቡ በደረቱ ለዘላለም ይሳብበትና ይንከባልለበት ዘንድ ሰው ዘላለማዊ አፈር ትቢያ መሆን
ቀረለት::
ይሁን እንጅ አሁን ባለንበት ምድር በጊዜያዊ ሁኔታችን ስላለን፥ ሰይጣን በእባቡ አካል ተሰውሮ፥ አፈር
የሆነውን አካል እንደሚልሰውና በደረቱ እንደሚሳብበት፥ በሸፍጠኞች ሰዎችም ተሰውሮ እንድንላስ እንድንበላ
ከማድረግ አይመለስምና ከዚህ አይነት ሕይወት ራሳችንን አድነን ሌላውም ከዚህ አይነት ሕይወት እንዲድን
ምስክር ለመሆን ተጠርተናል::

Details

Date:
April 24, 2022